NEME - your only gateway to info. on Islam in Ethiopia and Ethiopian Muslims
 
 
 
And hold fast, all together, by the rope which God (stretches out for you), and be not divided among yourselves. (Q003:103) The Believers are but a single Brotherhood: So make peace and reconciliation between your two (contending) brothers; and fear God, that ye may receive Mercy. (Q49:010)
NOTE: You need to have Unicode Geez font and keyboard installed on your PC to read the article below. Otherwise, go to our alternative page.

የኢትዮጵያ ሙስሊም ዑማ እና የመደራጀት አስፈላጊነት

M. Hassen

የኢትዮጵያ ዑማ ዛሬ ኢትዮጵያ ተብላ በምትታወቀዉ ሀገር ዉስጥ የሚገኘዉ ሕዝብ ሲሆን በቁጥር አነስ በዛ፤ በቆዳ ስፋትም ሰፋ ጠበብ እያለ ዛሬ ካለንበት ደርሥዋል።

ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ደግሞ ሙስሊም እንደሆነ ብዙ ምንጮች ያመላክታሉ። ታድያ እዉነተኛ እኩልነት፣ ፍትህና ድሞክራሲ የህዝቦችን በተለያዩ የህይወት ምእራፎች ላይ የመወከል እድል ማግኘትን የግድ አስፈላጊ ያደርገዋል። በአገራችን የምናየው ግን ከዚህ በጣም የተለየ ሁኔታን ነዉ።

ለዘመናት ሙስሊሞች በገዛ ሀገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ በመቆጠር ከፖለቲካው፡ ኢኮኖሚውና የማህበራዊ ህይወት አስተዳደሮች በፍፁም ተገልለው እናገኛቸዋለን። ለዚህም የተለያዩ ምክኒያቶች ቢኖሩም፤ ሙስሊሙ ሕብረተስብ ራሱን አደራጅቶ በተቀናጀ ሁኔታ ለማንነቱና ለመብቱ መንቀሳቀስ አለመቻሉ አንዱ እና ምናልባትም ዋነኛዉ ሳይሆን አይቀርም ብየ እገምታለሁ። በተለያዪ ጊዜያት በስልጣን ላይ የተቆናጠጡ አጼዎችና አምባ ገነን መሪዎች የሙሥሊሙን መብት እንዳሻቸው ለመርገጥ የበቁት እና ህልዉናውንም እስከመግፈፍ የደረሱት፣ የሙስሊሙን የመደራጀት አቅም እና ችሎታ በመምታት ነው።

ታድያ እኛም በአሁኑ ጊዜ በውጭ ሀገር የምንኖር ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ይህን እዉነታ ተገንዝበን በአንድ “ላኢላሀ ኢለላህ” ጥላ ስር መሰባሰብና መደራጀት ይኖርብናል። ይህም በአገር ቤት ካለው ታላቅ ሙስሊሞ ሕብረተሰብ እና ከዓለም አቀፍ  ማህበረሰብ ጋር ሊያስተሳስረን የሚችል ታላቅ ገመድ እና ኃይል መሆኑንም በመገንዘብ አስፈላጊነቱንም ከእስላም አንፃር ማየት አለብን።

እስላማዊ ድርጅት ከቤተሰብ፣ አካባቢ ጀምሮ ቀበሌ፣  ወረዳ፣ ክፍለ ሀገር፣ ሀገር፣ እያለ እስከ አህጉርና ዓለም አቀፋዊነት አንደዘለቀ የእስላም ታሪክ በህያዉነት ያስተምረናል። እኛም መደራጀትን ስናስብ መነሻ ማድረግ ያለብን በአካባቢያችን የሚገኘውን ሙስሊም ሕብረተሰብ ሆኖ ከሌሎች መሰል ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር በተቀናጀ ሁኔታ መንቀሳቀስ የረዥም ጊዜ ድርጅታዊ እቅዳችን ሊሆን ይገባል።

ለምሳሌ ከስዊድን ወይም ጀርመን ሀገር ተነስተን በተለያዩ የአዉሮፓ ሀገሮች ከዚያም ተሻግረን በሰሜን አሜሪካና አውስትራሊያ በአሲያ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪቃም ካሉ ኢትዮጵያዊኖች ጋር በመተባበር፤ ማንኛዉንም እንቅስቃሴያችንን ከአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር በማቀናጀት ዘለቄታ ላለው እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያካተተ ፍትህ፣ እኩልነትና ነጻነት መመሪያው ላደረገ አስትዳደራዊ ስርዓት መታገል ይኖርብናል።

የጀመዓ ሰላት ግደታ የሆነውን ያክል መደራጀት እና እንቅስቃሴያችንንም በተቆራኘ መልኩ ማድረግ ለሙስሊሞች እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ግደታም ነው። በመደራጀት የራስን፣ የማህበረሰብን እና የዑመትን ዕዉቀት እና እምነት (ኢስላምና ኢማን) ማሳደግ እና ማጠናከር ይቻላል። በሀገራችን የምናየውን የላሸቀ የእለት ተእለት የኑሮ ሁኔታ፣ ድህነትና ይህንም ሁኔታ በመጠቀም በሚሽነሪዎች አማካይነት ሙስሊሙ ከድኑ እንድርቅ ከዚያም ለማክፈር እየተደረገ ያለውን ጥረት ልንታደገው የምንችለው ራሳችንን አደራጅተን በተቀናጀ መልኩ መንቀሳቀስ ስንችል ብቻ ነው። የኢማን፣ የእዉቀት፣ የልማት እና የእድገትን ተግባራት እና ዓላማን በቀዳሚነትና በተቀናጀ መልኩ የያዘ ድርጅት ደግሞ ትክክለኛ እና እስላማዊ ነው። በዚህ መልኩ በመደራጀት እና ለተግባራዊነቱም በጽኑ በመታገል እስላማዊውን “ብዛት”ም ዘላቂነት ሊኖረው ወደሚችል “ጥራት”ቀየር እንችላለን፣ ኢንሻ አላህ።

ወንድሞችና እህቶች፦

እስላም ዛሬ ካለንበት የደረሰው በአባቶች ያላሰለሰ ጥረት እና ተጋድሎ እንደመሆኑ መጠን የዛሬውም ትውልድ ይህን ታሪካዊ አደራ በተጠናከረ ሁኔታና መሻሻል ያለበትን አሻሽሎ ስራቸዉንና ታሪካቸውን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግደታ አለበት። እዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት የሚሻ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያዊ ሙስሊሞችን ታሪክ፣ የትግል ገድልንና ያበረከቱትን አስተዋፆ በትክክል ማወቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ነው።

ስለ መደራጀት አስፈላጊነት እና በመልካም ስራ ላይ ዘውታሪዎች ስለመሆን ከቁርዓን እና ሀድስ ብዙ ትምህርቶችን ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ሱረቱ አል-ዐስር (የጊዜያት ምዕራፍ) እንውሰድ፦

“በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ በሆነው።

በጊዜያቱ እምላለሁ፤ ሰው ሁሉ በእርግጥ በከሳራ ዉስጥ ነው። እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሠሩት፤ በእውነትም አደራ የተባሉት፤ በመታገሥም አደራ የተባሉት ብቻ ሲቀሩ።” (ቁርዓን 103፡ 1-3)

በዚህ ምዕራፍ አላህ (ሱ.ወ) ወል-ዐስር ሲል በጊዜያቱ ማለ፤ ከዚያም ሰው ሁሉ በክስረት ዉስጥ እንደሆነ ገለፀ። ቀጥሎም ከእነዚያ ካመኑትና መልካሞችን ከሠሩት ካለ በኃላ እርስ በእርስ በመተጋገዝ፣ “በሀቅ መንገድ ላይ” በመያያዝና፤ ለአንድ አላማ ለጋራ ጥቅም በመሰባሰብ የሚታገሉ፤ ይህም ትግል መስዋዕትን የሚጠይቅ ስለሆነ በማንኛውም መልኩ በሚያጋጥማቸው እንቅፋት፤ መከራ እና ስቃይ ሳይበገሩ ለተነሱለት አላማ፤ ለቆሙለት እምነት በጌታቸው በመመካት “በትዕግስት” የሚታገሉ ብቻ ሲቀሩ ሌሎች ሁሉ በሁለቱም ዓለም ከሳራ ዉስጥ መሆናቸዉን “ወተዋሰዉ ቢል ሀቂ፣ ወተዋሰዉ ቢሰብር” በማለት ገለፀ። “ወተዋሰዉ ቢል ሀቂ” የሚለው ሀቅን መሰረት አድርገው በሀቅ የተደራጁ የሚል ፍች ሲወጣው፤  “ወተዋሰዉ ቢሰብር” ከሚለው ደግሞ ለድርጅቱ አላማ መሳካት እና ዘለቄታ ያለው ህልውና “ትዕግስት” እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለን።

ወንድሞችና እህቶች፦

የሰው ልጅ ዘመኑን ሁሉ ኑሮ በሀቅ ላይ ተሰባስቦ፤ እምነቱን ማጠናከርና በመደራጀት በሀቅ ነገር ላይ ዘውታሪ መሆን ሲገባዉ በከንቱ ሲባዝን ለክሥረት ራስን ከመዳረግ በላይ ታላቅ ጉዳት የለምና እኛም ይህን መልዕክት ልዩ ትኩረት ልንሰጠው ይገባናል፤ በተግባርም ለማዋል ዛሬ ነገ ማለት ወይም መሰላቸት የለብንም። የዚህች ዓለም ኮንትራታችን መቸ እንደምታልቅ እውቀቱ የለንም እና።

ወንድሞችና እህቶች፦

እኛ በዉጭ ሀገር የምንኖር ኢትዮጵያዊን ሙስሊሞች ራሳችንን በጥሩ ሁኔታ አደራጅተን፤ እንቅስቃሴያችንን ከሰፊው ሙስሊም ማህበረሰባችን ጋር በማቀናጀትና ተዛማጅ አላማ ያላቸው መሰል ድርጅትም ጋር ሰላማዊና ቀና ግንኙንት በመፍጠር ያለብንን ታሪካዊ አደራና እስላማዊ ግደታ ልንወጣ ይገባናል። ታድያ ለዚህ ቅዱስ ተግባር ስንነሳ ከጎናችን በመቆም አብረውን የሚታገሉ እንደሚኖሩ ሁሉ፤ በተቃውሞ ሊነሱብን፤ የወቅቱን ሁኔታም በመጠቀም አልባሌ ወሬዎችን ሊነዙ የሚችሉ ጠማሞች ሊጠፉ ስለማይችሉ፡ ሁሉንም በትዕግስት (ሰብር) እና በብልሀት (ሒክማ) በመያዝ ለምንቆምለት አላማ ግብ መምታት መታገል አለብን።

አላህ (ሱ.ወ) በእርሱ መንገድ (በሀቅ) ላይ በዘውታሪነት ቆመን የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች ሁሉ በትዕግስት እና በጥበብ በማሳለፍ የእርሱን ምንዳና ራህመት የምናገኝ ያድርገን።

ወአኺራ ዳዕዋና አኒል ሀምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን።

ወሰላሙ ዓለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱ።

This article is taken from the weekly "Friday Message" program co-organized by NEME & the Alemayan egroup. Would like to be included in their mailing list, then either follow the link geven to get registered or send a request to NEME (contact info.)
Recommended Readings

O N L I N E
L e c t u r e s

Every at kemishitu 4:00 se'at (Ethio)/ 21:00 cet/ 10:00 pm Mekka, Insha Allah. Learn more

- More Audio
- Ask the Scholar


Subscribe to the NEME egroup


Your are visitor

since 28/02/2004!

Network of Ethiopian Muslims in Europe, NEME © 2004-2005 All Right Reserved.
NEME has no the policy of editing or rejecting to publish the views of any participant, unless it incites hatred and the like, be it against individuals or groups. In that case, NEME deserves the right to deny space for such opinions in its site. NEME would like to remind all those who wish to make use of our service thus that we stand for understanding, respect and unity of the Muslim umma, and not for hatred, division, or sectorianism of any sort - all these are abhorred by the Amighty Allah (sw) and His final and beloved Prophet (saw). NEME promotes tolerance and peaceful co-existence of Ethiopians of all faith.

Views and opinions expressed in the articles we publish are that of the contributer(s) and do not necessarily reflect the position of NEME.